ሁላችንም የወደፊት እጣ ፈንታችን ላይ ያተኮርን ያሳለፍናቸውን ተመክሮዎች ለወደፊቶቹ ተግባሮቻችን ግብአት ለማድረግ የምንጥር ፍጡሮች ነን። ይህ ትኩረቱን ሁሉ ነገ ላይ ያደረግ እሳቤ የሚገለፅባቸው የትየለሌ መንገዶች ሲኖሩ በተለይ ዛሬ ደግሞ ዲጂታል ዓለም እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትልቅ ቦታ እየያዙ ይገኛሉ። ሮቦቶችን በፊት የሰዎች በነበሩ የሥራ ቦታዎች ላይ መጠቀም፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በናኖ ቴክኖሎጂ አማካኝነት እስክ እያንዳንዱ ሕዋስ ጥግ ዘልቆ መግባት፣ እና ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን የማስተላለፍን ለሰው ልጆች በተለይ የተጠበቀ የአስፈፃሚነት ስልጣን ራሳቸውን ችለው ለሚሠሩና ሲብስም ለሰው ልጆች የመጨረሻው አደጋ ሊሆን በሚችል መልኩ ራሳቸውን ሊያባዙ ለሚችሉ ሮቦቶች አሳለፎ መስጠትን የመሳስሉ ልበ ወለድ ትርክቶችና የሳይንስ ፋንታሲዎች ስል ወደፊታችን ያለን እይታና ሥዕል ላይ ተፅእኖ ያደርጋሉ፣ የፈጠራ ፋንታሲዎች ቢሆኑም ተመሳሳይ ሕልሞች እንድናይ ምክንያት ይሆናሉ። ስለ ነገአችን በምንሰማቸው እነዚህ ትርክቶች ለይ ያሉን አግራሞቶች ተስፋንና ሃሴትን ብቻ ሳይሆን ፍርሃትንና ጥርጣሬዎችንም ያካትታሉ። እዚህ ላይ ከራሳችን አእምሮ የሚመነጩና በፈጠርናቸው ቴክኒካል ሜዲያዎች አማካኝነት ምሥልና ትርክት የሚያገኙ ፈጠራዎች ተመልሰው አስተሳሰባችን ላይ ተፅእኖ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ህዋን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋልና ማርስ ላይ የመኖር እድል ለሳይንስ ልቦለድ ቅርብ ቢሆኑም ምድራችን ላይ ሊኖረን የሚገባውን አትኩሮት በመቀነስ የዛሬና አሁን ተጨባጭ ህይወታችን መዋቅር ውስጥ ይገባሉ። የእድገትና ስልጣኔ ጣራና ውጤት አለማችንን ለቆ ወድ ህዋ መሰደድ ከሆነና በዚህም የሰው ልጆች ፍላጎቶች ከተፈጥሮና ላመጣጣቸን ካለን የእስካሁን ግንዛቤ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከተካደ ምድራችንን ወሳኝ አደርጎ የማየት እሳቤ እየተሸረሸረ ይሄዳል። በሳይንስና ጥበብ አማካኝነት በአእምሮአችን የተወለደው ምናባዊ ዓለም ከምድራችንና ከሷ ጋር የሚያያዙ ችግሮች ጋር የምናደርገውን ግብግብ አላስፈላጊ በማስመሰል የስሜቶች ውጣ ውረድ የሌለበት፣ አልጋ ባልጋ የሆነና በሂሳብ ስሌት ተቀምሮ የሚቀመጥ የመኖር ትርጉም ቃል ለመግባት ይዳዳዋል።
የዚህ አይነቱ ስለ ሰው ልጆች የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርብ ትንቢት ሃይሉ በዋናነት የሚመነጨው ልክ እንደ ካፒታሊዝም በተለያዩ ተፅእኖ ፈጣሪ ሃይሎች አማካኝነት የሰው ልጆች የእድገት ጉዞ አማራጭ የለሽ መዳረሻ እየተደረገ መቅረቡ ነው። ግን ይህ የነገአችን ትንቢት ምክንያቱ የተለመደውና የሰው ልጆች ተፈጥሮ የሆነው ለራስ ተግባር ሃላፊነት ያለመውሰድ ዝንባሌ ይሆን? ችግሮችን እየፈጠረ ያለውን በግለሰብ፣ ማህበረሰብና ቴክኖሎጂ መካከል ያለ የሃይል አሰላለፍ ላለመፈተሽ በዚህም ለተወሳሰቡ ና ብዙ አትኩሮታችንን ለሚሹ ተግዳሮቶች የማይጨበጡ የፋንታሲ መልሶች በመቸር የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን ማህበረሰባዊና ዲሞክራሲያዊ ሃላፊነቶችን መሸሽ ይሆን?
ገና ስላልተገኘ የልበ ወለድ ዓለም እየተጠበብን በርግጠኝነት ያለችንንና ብቸኛዋን የመኖሪያ ምድራችንን መበደል ትልቅ ጥፋት አይደለምን? ፕላን ቢ ን ፈልገን ሳናገኝ ፕላን ኤ ን መጣል ሞኝነት አይደለምን? እያንዳንዳችን በመኖራችን ብቻና ከዚያ ደግሞ በአኗኗር ዘይቤአችን ለምድራችን መበላሸት እንደምናዋጣ ማወቅ ይገባናል። ስለሆነም የኢኮሎጂን ጥበቃ ከዋነኞቹ የሞራል ግዴታዎቻችን አንዱ ማድረግ ወሳኝ ነገር ነው። ነገሩ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነው። የእንስሳትና እፅዋትን፣ የተራሮችና ወንዞችን፣ የባህሮችና ጫካዎችን መብቶች ደንግጎ በውዴታ መጠበቅ ከተፈጥሮ ጋር ያስታርቀናል። የሰው ልጆች ሁሉ ተባብረን ከሃላፊነቶች ሁሉ ትልቁ የሆነውን ተፈጥሮን የመንከባከብና የመጠበቅ ሥራ መተግበር ግድ ይለናል።
እያንዳንዱ የሰው ፍጡር ተፈጥሮ የቸርችው ትልቅ የታመቀ አዎንታዊ ሃይል አለው። ይህንን እምቅ ሃይል በእውቀት፣ በተሞክሮና በጥበብ እያገዙ ምቹ የሆነ የመኖሪያ ከባቢን ለመፍጠር ምድራችን የገጠሟትን ችግሮች በጥልቅ መረዳትና እነዚህንም ችግሮች ለመቅረፍ ቁርጠኝነትና ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። የፕሮጀክት ዩቶፒያም ተልዕኮ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለአዲስ የሰዎች ሉዓላዊነት መፈጠር የሚበጁ መንገዶችና ዘዴዎችን በመጠቆም የዘመኑ ግኝቶች የሆኑትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዋናነት ተፈጥሮን ማገዣና መንከባከቢያ የሚሆኑበትን ስነ ልቦናዊ ድባብ ማመቻቸት ነው። የወደፊቷን ለሁላችንም ቦታ የምትሰጥ ብሩህ ዓለም ለማምጣት ጅምሮች፣ ስትራቴጂዎችና ጥረቶች ዛሬውኑና በያለንበት በግልፅ መታየት አለባቸው። አንተም፣ አንቺም፣ እኔም ዲሞክራሲን እየተገበርን ወደፊት እንዴት አብረን መኖር እንደምንፈልግ የምናሳይበት መድረክ ነው። በፕሮጀክት ዩቶፒያ! መልስ የምንሰጠው ወደፊታችን ምን መምሰል አለበት ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው!
ረቡዕ ሜይ 29 ቀን 15 ሠዓት ኑረንበርግ ሎረንዘር ፕላትስ
አርብ ሜይ 31 ቀን 15 ሠዓት ፉርት ሱድ ስታድት ፓርክ
ቅዳሜ ጁን 1 ቀን 15 ሠዓት ኤርላንገን ሽሎስፕላትስ